የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስር የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች ማዕከል የሥራ አፈጻጸምን ተመልክቷል።
በምልከታው ወቅትም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አለሙ እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት የማዕከሉን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የህክምና መስጫ ክፍልን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ በማዕከሉ የሚታዩ የአገልግሎት ክፍተቶች ተለይተው የቀረቡ ሲሆን፣ በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ያመላከቱ ሲሆን የጊቢውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋልና ምድረ ግቢው ዘመኑን የሚመጥን ምቹ አካባቢ ማድረግ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴዋ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ቢሮው ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር ለሴቶች ተጠቃሚነት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለህፃናትና ለማህበራዊ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት በመስጠት የታቀዱ እቅዶችን በውጤታማነት እንዲያስፈጽም አሳስበዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ቢሮው ያሉትን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠል ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ እንዲያዘምን አፅንኦት ሰጥቷል